Tuesday, April 2, 2013

አሐዱ


ሰላም ጤና ይስጥልኝ ለተከበራችሁ የድረ-ገፅ ተከታታዮች፡፡ እኔም ሲያደርጉ አይቼ ለምን አልሞክርም በሚል የየዋህ ድፍረት ተነሳስቼ ሀሳቤን፤ አይቼ፤ ሰምቼና አንብቤ የወደድኩትንና የጠላሁትን የማጋራበትና የምተነፍስበት ብሎግ ወየም የጦማር ጀምሬአለሁና አብሮ ያዝልቀን፡፡
የመጀመሪያውን የዚህን ጦማር ፅሁፍ የተዋስኩት ከዶክተር እጓለ ገብረዮሐንስ መጽሀፍ ነው፣ በሁለት ምክንያቶች ምክንያት አንድም የምሰራበት መስሪያ ቤት የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ብሎም የጥናትና ምርምር ተቋም ስለሆነ፤ ሁለትም የትምህርት ጥራትና ሥነ ምግባራዊ ትምህርት እጥረት ሀገሬን ማነቆ ሆኖ እያሰቃያት እንደሆነ በመመልከቴ ነው፡፡

ሥነ ምግባራዊ ትምህርት
ሰውን ጥቅም፣ ተድላ፣ ደስታ ብቻ ተፈላላጊ አድርጎ በመመልከት፤ ይህንኑ ምኞቱን የሚያረካበት
ትምህርት ብናቀርብለት የሚጎዳ የሚበደል እንጂ የሚጠቀም አይደለም:: ምክንያቱም ሰዎች በመላ
ለዚህ ነገር ብቻ ቢሰለፉ በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ያለው ውድድር መልኩን ለውጦ ያለመጠን
አስቸጋሪና የሚያፋጅ ሊሆን ይችላል:: በተለይም ይኸ እንዲህ ያለ ጥቅምን ብቻ የሚመለከት
ትምህርት የሚያስገኘው ጠባይ ከሥልጣን ጋር የተገናኘ እንደሆነ ነገር ጨርሶ ሊበላሽ ይችላል::
ለኔ ማለት ይሰፍናል:: ሥልጣን የግል ንብረት ማዳባሪያ ወይም መከላከያ መሣሪያ ይሆናል::
ሌላው የመኖር መብት ያለው አይመስለውም:: ‹‹መኑ ዘከማየ›› ማን እንደኔ በማለት ራሱን የነገሮች
ሁሉ መወሰኛ መዳልው መስፈርት ያደርጋል:: እንዲህ ያለ የመንፈስ ሁኔታ ወዴት እንደሚያደርስ
የታወቀ ነው:: ሐተታም አያሻ፤ በዚህ አንጻር የሥነ ምግባርን ግዴታዎች የትምህርት መሠረት
በማድረግ የሰው ዝንባሌዎች በሙሉ እንዲያድጉ መርዳት ከእውነተኛው የትምህርት ዓላማ
ያደርሰናል:: የተሟላ መንፈስ ያለው ሰውነት ለማግኘት ይቻላል:: ያንጊዜ ለጥቂት ወይም ለቅርብ
ተድላ ደስታ ከማሰብ አልፎ በተለይ የማርካት ኃይል ያለው ንጹሕ የመንፈስ ደስታ መኖሩን ይረዳል::
እንዲህ ያለውን አርኪ ደስታ የቀመሰ ሰው ‹‹አንጽሖ መንፈስ መንኖ ጥሪት መጥዎተ ርእሰ››
ለሚባሉት ከፍተኛ የሥነ ምግባር አኃዞች ልዩ መስሚያ ጆሮ አለው:: ለሕይወት ዋጋዎች ሁሉ
በትጋት ያስባል:: ለእውነት ይከራከራል:: ለነፃነት ይታገላል:: ለትክክል ፍርድ ይሟገታል:: ለውበት
ይደነግጣል፣ ያደንቃል:: ይህ ከማናቸውም ጥቅማዊ ነገር የበለጠ ደስታ በቁዔት ያስገኝለታል::
ሂዩማኒስቶች ስለትምህርት ዓላማ ያላቸው አስተያየት ይህ ነው:: ለዘመናችንም ትምህርት መሪ
ሐሳብ ይሆን ዘንድ ከዚህ ያነሰ አንመኝለትም:: የቀድሞ ዘመን ሶፊስቶች ያቀረቡት የጥቅም
አገልጋይ የሆነ አሳሳች ትምህርት በጊዜአችንም ስሙን ለውጦ ‹‹ፕራግማቲዝም›› በሚባል የአሜሪካ
ፍልስፍና አማካይነት ዘመናዊ ዳባ ለብሶ ወደየ እልፍኝ አዳራሹ ለመግባት ያንኳኳል ‹‹ዳባና ቆዳ
ከለየን ዘገየን::›› ማለት የሚገባን እዚህ ላይ ሳይሆን ይቀራልን?››
‹‹የትምህርት ዘይቤ›› (1956) ከተባለው የዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ የተጠቀሰ

1 comment:

  1. Its a good start! Am proud of u and keep up the good work.

    ReplyDelete