ለዛሬ የመረጥኩት ርዕስ በጣም ሰፊ መሆኑን ብረዳውም ግን አንብቤም ሰምቼም ግራ የገባኝና ያልተመለሰልኝ ጥያቄ ስለሆነ
ለምን የማውቀውን ያህል ፅፌ፤ ያልገባኝን ጠይቄ አልማርም ብዬ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ (ሁሌም ማለት ይቻላል) የመንግስትንና የተቃዋሚዎችን የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በተመለከትኩ፣ ባዳመጥኩና ባነበብኩ
ቁጥር ግራ የሚገባኝ ሁለቱም የሚያተኩሩት በኢትዮጵያ ላይ ይሁን እንጂ እርስበርስ የሚተያዩት በተለያየ መነፅር ነው እስገባኝ ድረስ፡፡
በአጭር አማርኛ፣ ተቃዋሚዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንደሌለ ማለትም ነፃ ምርጫ፣ ነፃ ፕሬስ፣ ወዘተ … የለም” ሲሉ የኢትዮጵያ
መንግስት ደግሞ በበኩሉ “ኢትዮጵያ በድርብ አኃዝ እያደገች ነው፣ የምግብ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አኃዝ ወረደ፣ ከ20
ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሀገሮች ተርታ ትሰለፋለች፣ ወዘተ…” የሚሉ ወሬዎች (የሸገሮችን ቃል ልዋስና) ነው
የምታዩት፡፡ እኔ እንደ ገባኝ የሁለቱ አለመግባባት መሰረቱ በአንድ ላይ ሲጠቀለል ከልማትና ከዴሞክራሲ የቱ ይቅደም የቱስ ይከተል
የሚለው ላይ ይመስለኛል፡፡
የዴሞክራሲ ቲፎዞዎች
ይህን ጥያቄ ሲመልሱ “ህዝብ እንዲያስተዳድረው የፈለገውን ከመረጠ፣ የሚሰማውን በነፃነት በአደባባይ ሳይሳቀቅ ከተናገረ፣ ህዝቡ ይመቸኛልና
ያዋጣኛል የሚለውን የልማት መንገድ ተከትሎ ሀገሩን ያለማል፣ ከልማቱ የሚገኘው ኃብት ደግሞ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለህዝብ ይከፋፈላል፣
ምክንያቱም ተጠያቂነትና ግልጽነት (Accountablilty & Transparency) ስለሚኖር ሀገር በተፈለገው ፍጥነት ማደግ
ትችላለች፡፡” ብሎ ነጥባቸውን ጠቅለል ማድረግ ይቻላል፡፡
የልማት አቀንቃኞች
በፊናቸው እንዲህ ሲሉ ይሞግታሉ “ህዝብ ርቦት ምርጫ ምረጥ ቢሉት እገሌ ዳቦ አይሆነኝ እንጀራ ነው የሚለው፣ ህዝብ ርቦት የመናገር
ነጻነት ስላለህ የፈለከውን ተናገር ብትሉት ኡኡኡ ራበኝ ነው ሊለው የሚችለው ያለችውን ኃይል አሟጦ፣ ስለዚህ ለራበው ህዝብ ነፃ
ምርጫና ነፃ ፕሬስ የምትሉት የምዕራባውያን ቀረርቶ ሳይሆን የሚያስፈልገው በመጀመሪያ የተራበ ሆዱን ማጥገብና ነገን እንዲያይ ማድረግ
ነው፡፡ በርግጥ ሰው እየጠገበ ሲሄድ ደግሞ በነፃነት የመናገር ፍላጎት ሊያድርበት ስለሚችል የተወሰነ ነፃነት መስጠት ነው፡፡” እያሉ
እነ ቻይናን እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡
ሁላችንም ልናነሳ የምንችለው
ጥያቄ ለምን ሁለቱም በጥምረት (Simultaneously) አንድ ላይ ሆነው
ጎን ለጎን ለምን አይሄዱም ነው፡፡ አሁን አለም ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የምንረዳው ሁለቱንም እኩል አብሮ ማስኬድ እንደማይቻል
ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ሲሞክሩ በዴሞክራሲ ግንባር ቀደም ነን የሚሉት ምዕራባውያን በተለይም አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ኢኮኖሚያቸው
አዘቅጥ ውስጥ ሲገባ ዴሞክራሲን ከስም በላይ አታውቀውም የምትባለው ቻይና ግን አሁንም ዓለምን በሚያስገርም ፍጥነት እያደገች ከመሆኑም
በላይ ለነ አሜሪካ እያበደረች ነው፡፡
አሁን አሁን እየሰማን
ያለው ስለ አፍሪቃ የሚወራው መልካም ዜና መምጣት የጀመረው በተለይም ቻይና ወደ አፍሪቃ ከገባችና የመሰረተ ልማት ስራዎች ከተስፋፉና
ሐገሮች በውስጥና በውጭ የሚያደርጉት ንግድ ከጨመረ ወዲህ ነው የሚሉ አሉ፡፡ አፍሪቃ በታሪኳ በጣም የተራጋጋችበት ወቅት ነው ሲባል
እየሰማን ነው ይህ ደግሞ ሀገሮች እያስመዘገቡት ካለው ልማት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
በሌላኛው ጥግ ያሉ
ተሟጋቾች የአረብ ፀደይ (Arab Spring) ተብሎ የተጠራውን
የአረቡን ዓለም ያናወፀውን የህዝብ አመጽ በማንሳት እንዲህ እያሉ ይሞግታሉ “የአረብ ሀገራት በብዛት ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ሀብታም
ሀገሮችና ለህዝባቸው “መሰረታዊ” ፍላጎቱን የሚያሟሉ ቢሆኑም በዕምነትና በዘር ሽፋን ባለስልጣናቱ ህዝቡን ሲበዘብዙትና ሲጨቁኑት
ስለኖሩና ፍትሕ ስለነፈጉት ህዝቡ ከስልጣናቸው ፈነገላቸው፡፡ ስለዚህ መንግስታቱ የተሻለ ሕይወት ህዝቡ እንዲመራ ቢያደርጉትም የመናገርና
የፈለገውን የመምረጥ መብቱን ስላላከበሩለት ዞር በሉ አላቸው፡፡”
በሌላኛው የጠረጴዛ
ጥግ ደግሞ በተለይም የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ሁለቱን ምን አገናኛቸው ባይ ናቸው፡፡ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ጥያቄ ሲሆን ልማት ደግሞ የኢኮኖሚ
ጥያቄ ነው ስለዚህ ሁለቱንም በተለያየ መነፅር ለያይተን ነው መመልከት ያለብን ባይ ናቸው፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያን
ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባው የትኛው ነው፡ ልማት ወይስ ዴሞክራሲ? የሚለውን ጥያቄ
በቅንነት (Rationally) ብንወያይበት እኔ
ማለፊያ ነው ባይ ነኝ፡፡
ፍሬዘር ማሩ
No comments:
Post a Comment