ይህ በልዑል የኢትዮጵያ
መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን በራሳቸው ማተሚያ ቤት ታተሞ በመጋቢት 8, ቀን 1916 ዓ.ም. ለንባብ የበቃው የጃንሆይ የምክር
ቃል በጣም አዝናኝ፣ አስተማሪና በወቅቱ የነበረውን የማሕበረሰቡን አስተሳሰብና አኗኗር የሚያመላክት ሆኖ ስላገኘሁት ላካፍላችሁ ወድጃለሁ፡፡
ለትምህርትም ቢሆን፣
ለንግድም ቢሆን፣ ወይም ከመንግሥት ተልኮም ቢሆን ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር የሚሔድ ሰው ሁሉ ይህን የምስክር ቃል ማንበብ ይገባዋል፡፡
በመርከብም፤ በባቡርም፤
በሆቴልም በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ለማድረግ የማይገባ፡፡
1.
በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ልብስን አንፍጫ ላይ ማድረግ ወይም ራስን መከናነብ
አይገባም፡፡
2.
ጧት ጧት ራስን ፊትን ሳይታጠቡ ወደ ውጭ መውጣት አይገባም ደግሞ በጥርስ ቡርሽና
በሳሙና ጥርስን አፍን መታጠብ ነው፡፡ ደግሞ በጥፍር ውስጥ እድፍ እንዳይታይ በየጊዜው ማውጣት ያስፈልጋል፡፡
3.
በትልልቅ ሰዎች ፊት ይልቁንም በወይዛዝር ፊት ጥርስን መፋቅ ከጥፍር ውስጥ እድፍ
ማውጣት አይገባም፡፡
4.
ከትልልቅ ሰዎች ጋራ ይልቁንም ከወይዛዝር ጋራ ሲነጋገሩ እግርን አጣምሮ መቀመጥ
መጨጊያ ተንተርሶ በጎድን መጋደም አይገባም፡፡
5.
ትልልቅ ሰዎች ይልቁንም ወይዛዝሮች ለመጠየቅ በመጡ ጊዜ ከወምበር ተነስቶ ቆሞ አክብሮ
መቀበል ይገባል፡፡ ተቀምጦ እንግዳ መቀበል ግን ትልቅ ነውር ነው፡፡ ደግሞ ትልቅ እንግዳ ተቀምጦ ሳለ እርሱን መነጋገር ትቶ ጋዜጣ
ማንበብ ጽሕፈት መጻፍ አይገባም፡፡
6.
እንግዳ ተቀምጦ ሲነጋገር ሰዓት አውጥቶ ማየት ሒድልኝ ከማለት ይቆጠራል፡፡ ነገር
ግን ወደ ሰው ቤት ሔዶ ጉዳዩን የሚነጋገር ሰው በንግግሩ መካከል ሰዓት አውጥቶ ቢያይ እርሱ ለመሄድ መቸኮሉን ያስረዳልና ነውር
የለበትም፡፡
7.
በመብልና ባካሄድ በመቀመጥም ጊዜ ወይዛዝርን መቅደም አይገባም በስፍራውም ያለው
ወምበር ለሁሉ የማይበቃ የሆነ እንደሆነ ወምበሩን ለወይዛዝር ለቆ መቆም ይገባል፡፡
8.
በቤተ መንግስትም ቢሆን በፋብሪካም ቢሆን የሚታይ ነገር ለማየት በመግባት ጊዜ ልብን
አንቅቶ እንደዋዛ ዓይንን ጣል አድርጎ ማየት ነው እንጂ ከባላገር እንደመጣ ሰው ዓይንን እያቅበዘበዙ ማየት አይገባም፡፡
9.
በሰውም ፊት ቢሆን ለብቻም ቢሆን አክ ብሎ አክታ ወደ ምድር መትፋት አይገባምና
በቀስታ አክ ብሎ በመሐርም መቀበል ነው፡፡ በመናፈጥም ጊዜ አፍንጫን በመሐርም አጥብቆ ይዞ በቀስታ መናፈጥና ወደ ምድር መጣል አየገባም፡፡
10.
በምግብ ጊዜ ወይም በሌላ ጊዜ ብዙ መጠጥ መጠታት ነውር ነው፡፡ የወይን ጠጅም በመጠጣት
ጊዜ ውኃ እየደባለቁ መጠጣት ነው እንጂ ብቻውን መጠጣት ሰውነት ይጎዳል፡፡ አረቄ መጠጣት ለትልቅ ሰው በጭራሽ ቢቀርበት መልካም
ነው፡፡ ለመተው የማይችል ሰው ግን አንድ መለኪያ ብቻ ይጠጣ እንጂ ከዚህ የበለጠ ቢጠጣ ነውር ይሆንበታል፡፡
11.
በቤተ መንግስትና በሌላም በትልልቅ ስፍራ በቤተ ክርስቲያንም፣ በትልልቅ ሰዎችም
ፊት ቀስ ብሎ በእርጋታ መሄድ ነው እንጂ ጫማ ድምጥ እስቲሰማ እየረገጡና እየተገላመጡ መሄድ አይገባም፡፡
12.
ከትልቅ ሰው ጋራ በመነጋገር ጊዜ በለዘብታና በቀስታ ቃል መነጋገር ነው እንጂ እየጮሁ
መነጋገር አይገባም፡፡ በመሳቅም ጊዜ ጥርስን ፍግግ ፍግግ እያደረጉ መሳቅ ነው እንጂ በውጭ እስቲሰማ ድረስ እየተንከተከቱ መሳቅ
አይገባም፡፡
13.
በማናቸውም ጊዜ ቢሆን በመሸታ ቤትና በጋለሞታ ሰፈር ተቀምጦ መታየት ትልቅ ነውር
ነው፡፡
14.
ባካሄድም ባቀማመጥም ጊዜ ባለማዕረጉን ማክበር ነው እንጂ ትንሽ ማዕረግ ያለው ትልቅ
ማዕረግ ያለውን መቅደም አይገባም፡፡
15.
በንግግር ጊዜ የተጠየቀው ሰው ሳይናገር ያልተጠየቀው ሰው ለመናገር አይገባውም፡፡
በነገሩም መካከል ማሰናከል አይገባም፡፡
16.
ወንዶች ወደ ሴቶች ሰገራ ቤትና መታጠቢያ ቤት እንዳይገቡ ክልክል ነውና ስፍራውን
ተጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
17.
ከመርከብ በመውረድ ጊዜ ለመርከብ አገልጋዮች እንደተቻለ ጥቂት ጥቂት ገንዘብ መስጠት
ያስፈልጋል፡፡
18.
በመርከብ ውስጥ ሙቀት በጸና ጊዜ ነፋስ የሚያመጣውን የአሌክትሪክ መኪና ባስፈለገ
ጊዜ መዘወር ነው፡፡ ባላስፈለገና ወደውጭ በመውጣት ጊዜ ግን መኪናውን አቁሞ መውጣት ይገባል፡፡
19.
ወደ ሰገራ ቤት በመግባት ጊዜ መዝጊያውን ከወደ ውስጥ አጠንክሮ መዝጋት ያስፈልጋል፡፡
ጉዳይንም ጨርሶ በመውጣት ጊዜ ባጠገብ በተሰቀለው ውኃ እድፉ እንዲወርድና ንጹህ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እድፉን በውኃ ንጹህ ሳያደርጉ
ከሰገራ ቤት መውጣት ትልቅ ነውር ነው፡፡ በኃላም መዝጊያውን ክፍቱን
ትቶ መውጣት ነው እንጂ ዘግቶ መውጣት አይገባም፡፡
20. በመርከብ ውስጥ ባዳራሹ
(ሳሎን) ወይም በመናፈሻው ስፍራ፣ በትልልቆች ሰዎችና በወይዛዝር ፊት ነጠላ ጫማ አድርጎና የሌሊት ልብስ ለብሶ መታየትና መሄድ
ትልቅ ነውር ነው፡፡
እንዲህ እንዲያ እያለ
ይቀጥላል እኔ በበኩሌ ተመችቶኛል እናንተም ተመችቷችኋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ምክሩን ሙሉ በሙሉ ቢያነቡት ጃንሆይ በእያንዳንዱ ነገራቸው ምን ያህል ጠንቃቃ እንደሆኑ መረዳት
ይቻላል ባይ ነኝ፡፡
No comments:
Post a Comment