Friday, April 5, 2013

“አንድ ሺ ከአንድ ሌሊቶች”


ከፊታችን ያሉት ለብዙዎቻችን የዕረፍት ለጥቂቶች ደግሞ የስራ ቀናት እንደመሆናቸው ፤ ለምታርፉት እንደ ተጨማሪ መዝናኛ እንዲሆላችሁ፣ በስራ ለምታሳልፉት ደግሞ በሻይ እረፍታችሁ አንብባችሁ ዘና ትሉ ዘንድ አስቤ የጋሽ ስብሀት ገብረእግዚአብሔርን አንድ ሶስት ወጎች ላጋራችሁ፡፡




ምስጋና ካስፈለገማ ሰጪ ነው ማመስገን ያለበት

አንድ

ዛሬም ከሱፊዎች (በአላህ መንገድ የሚጓዙ መንፈሳውያን ሙስሊሞች) አንድ ትረካ እንጋብዛችሁ:: አንድ ሰውዬጋ አንድ ጓደኛው መጣናእገሌ ችግር አጋጥሞታልና አንድ መቶ ዲናር አምጣ-ስቲ ልውሰድለትሰውዬው ሀብታም ባይሆንም አውጥቶ ሰጠው:: ተቀብሎ ሄደ:: ሌላ ቀን ያው ጓደኛው መጣናእገሌ ዛሬም ችግር አጋጠመው:: እስቲ ዛሬም አንድ መቶ ዲናር ካለህ ስጠኝ ልውሰድለትሰውየውም ፈላልጐ አምጥቶ ሰጠው:: ተቀብሎ ሄደ:: ሶስተኛ ቀን ያው ጓደኛው አሁንም መጣናባይገርምህ ዛሬም እገሌ ችግር ደረሰበት:: ሌላ መቶ ዲናር ፈልግለት:: ምስኪን ሰውዬ!” ሰውየው እንደምንም ፈላልጐ አገኘለትና ሰጠው::
ጓደኝየው ተቀብሎ ሊሄድ ሲልስማኝ እንጂይለዋል ሰውዬው:: “ሀብታም አለመሆኔን ታውቃለህ:: አከታትለህ ሶስት ጊዜ መቶ ዲናር ስትወስድ አንድ ጊዜንኳ አላህ ይስጥልኝ አይባልም እንዴ?” “!...” ይላል ጓደኝየውነገሩ ስለምስጋና ነው? ምስጋና ካስፈለገማ ሰጪ ነው ማመስገን ያለበት::” (ተቀባይማ ያመሰግናል- ሰጪንም አላህንም ይበልጥ ግን ማመስገን የሚገባው ሰጪ ነው:: ቢኖረው አይደል መስጠቱ? ባይኖረውማ እሱ ራሱ ተቀባይ ነበር የሚሆነው:: ለዚያውም ሰጪ ቢያገኝ ነው:: ስለዚህ በቂ ሰጥቶት ሰጪ ለመሆን ያበቃውን አላህን ያመሰግናል::)

ልብህ እስኪጠፋ እንድትወደኝ ፈልጌ

ሁለት

ከቆላ በረሀ አገር ጨርቃ ጨርቅ፣ ቅመማ ቅመም፣ እጣን፣ ልዩ ልዩ ቅጠላ ቅጠልና የሥራ ሥር መድኃኒት፣ መርፌ፣ ምናምን የተጫነ ግመል እየጐተተ በደጋው አገር ከመንደር መንደር ከቤት ቤት እየተዟዟረ የሚነግድ አንድ ሰውዬ ነበረ:: አንድ ቀን ይህን ሰውዬ አንዱዋ ሴትእናንተ ብዙ አይነት መድኃኒት ታውቃላችሁትለዋለች:: እናውቃለን ሲላትባሌን በጣም በጣም እንዲወደኝ እፈልጋለሁ:: መድኃኒት ታውቃለህ ወይ? አዎን አውቃለሁ:: ሽጥልኝ:: ዋጋው ውድ ነው:: ይሁን:: ይሸጥላታል:: በእህል ቀላቅለሽ አብሊው:: ሲበዛ ደስ ይላትናቆየኝ ቆንጆ ሽሮ እየሠራሁ ነው በልተህ ትሄዳለህ ርሚጦ በርካታ ምናምን ደረቅ የጉዞ ስንቅ መብላት የሰለቸው ነጋዴ እጅግ ይደሰታል:: ደጃፉ አጠገብ ካለው ዛፍ ስር ጥላ ውስጥ ግንዱን ተደግፍ ሽሮው እስኪደርስለት ይጠብቃል:: ደረሰለት:: ቀረበለት:: ለዓይን እንኳ ደስ ማለቱ! እሷ ወደ ቤት ተመልሳ ገባች:: እሱ ጥስቅ አርጐ በላ:: እናአንቺ!” ብሎ ተጣራ:: ወጣች:: “ያን የሰጠሁሽን መድኃኒት በሽሮው አበላሽኝንዴ?” “አዎን!” “ለምን?” “ልብህ እስኪጠፋ እንድትወደኝ ፈልጌ” “በይ ጠፋልሽ አንች እርኩስ ከይሲ!” አላትና ፍንግል አለ:: ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው አለ:: እስቲ ፍቅር ሸጥኩልሽ ብሎ ሞት ይሸጥላታል? እሷስ በምን አሰበችው? ሴት ብልህ በመሆኗ? ወይስ ነጋዴው ቀኑ በመድረሱ? ወይስ ምን?

ምድር ቤቱን ስጠው አላችሁኝ ሰጠሁት

ሦስት

እነሆ ሁለት ቂሳ ባጭሩ አብዱልቃዱር ጅላሊ ከባግዳድ ነው የመጡት ይባላል:: እሮብ በስማቸው የሚከበርላቸው:: ለአያሌ ዓመታት ሲያገለግሉዋቸው የኖሩትን ሁለት ተከታዮቻቸውን የሚያሰናብቱበት ጊዜ ደረሰ:: የትኛውን ወዴት እንደሚልኩትና እዚያስ ምን እየሰራህ ትተዳደራለህ እንደሚሉት ለማወቅ በሌላ አባባልም የሁለቱን ዋጋ ወይም ክብደት ለመመዘን እንዲህ አደረጉ:: ለሁለቱም አንድ ዶሮ ሰጡዋቸውናለየብቻችሁ ሂዱና ዶሮዋን እኔ በሌለሁበት ስፍራ አርዳችሁ አምጡልኝ አሉዋቸው:: ተቀብለው ቢላ ቢላቸውን ይዘው ሄዱ:: አንደኛው ሄዶ ዶሮዋን አርዶ መጣ:: ሁለተኛው ግን ቆይቶ ዶሮዋን ሳያርዳት ይዟት ተመለሰ:: “ምነው አላረድካትቢሉት እርስዎ የሌሉበት ቦታ አጣሁአላቸው:: (ሌላውን ለአንባቢ እንተዋለን::) አንድ ነክናካ (ነፍናፋ) ሼህ ፎቅ ቤታቸው ውስጥ ይኖሩ ነበር:: ደርጉ መጣና የቤታቸውን ፎቁን ተወረሱና የቀበሌ ባለሥልጣን ገባበት:: ለሳቸው ምድር ቤቱን ተወላቸው:: እሳቸውም ቤቴን አስመልሱልኝ፤ ልወረስ አይገባኝም እያሉ ቀበሌ ጽህፈት ቤት እየተመላለሱ ሊቀ መንበሩን አሰለቹት:: ማመልከቻ ይጻፉ ሲላቸውእኔ ምኑን አውቄ እጽፈዋለሁ? አንተው ፃፍ ፃፍ አርግና እንደሚሆን አርገህ አስመልስልኝ:: እሱም አላስመለሰላቸውም እሳቸውም መመላለሳቸውንም አልተው:: በመጨረሻምወይም ፎቁን እርስዎ ይውሰዱትና ምድር ቤቱን ለሱ ይስጡትአላቸው:: “እንዲያ ካላችሁኝ መልካም!” ብለውት ሄዱ:: በነጋታው ጧት ፎቃቸው ውስጥ ይኖር የነበረው ባለሥልጣን ሞቶ ተገኘ:: ሊቀ መንበሩ መጥቶምን ተደረገ እነ ሼህ?” ቢላቸው ምድር ቤቱን ስጠው አላችሁኝ፤ ምድር ቤቱን ሰጠሁትአሉት::

ስብሐት ገብረ እግዚአብሔርአንድ ከአንድ ሌሊቶች” (1987)

No comments:

Post a Comment