Monday, September 9, 2013

ኢትዮጵያዊ ሕልም



ባልሳሳት ከትላንት ጀምሮ ይመስለኛል Zone9ers (ዞን 9ኞች) “ኢትዮጵያዊ ሕልም፣ ኑ አብረን እናልም!” በሚል መሪ ቃል ወይም ሃሽታግ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሚጠቀሙባቸው የማህበራዊ ድረ-ገጾች ማለትም ፌስቡክና ትዊተር አማካይነት ለአዱሱ ዓመት እናም ከዚያም ለጥቀው ላሉት ዓመታት ሀገራዊ ህልሞቻችንን እንድናጋራ ጥሩ ርዕስ አምጥተው ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይም በውጭ የሚገኙት ህልማቸውን እያጋሩን ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ብዙ ህልሞች አንብቤያለሁ ደስ ሚሉ፣ የሚያሳዝኑ፣ የሚያስከፉ፣ ብሎም የሚያሳፍሩ ናቸው፤ ለማንኛውም የኔ ኢትዮጵያዊ ሕልም ይሄ ነው፡፡
ኢኮኖሚው
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሳይሳቀቅ ቢያንስ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት እንዲችል፤
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔ የሚለውና በኃላፊነት የሚወጣው ስራ እንዲኖረው (በግሉም ተቀጥሮም ሊሆን ይችላል)፤
የዘይት ዋጋ አስወድዶ የጤፍ ዋጋ ያስወደደውን ገበሬ የሚራገም ነጋዴ ጠፍቶ ሕዝብነቱ ሁሌም የሚታወሰው ነጋዴ እንዲፈጠር፣
ግብር ግዴታዬ ሳይሆን መብቴ ነው ብሎ የሚከራከር ነጋዴ ተፈጥሮ ማየት፣
የተፎካካሪዬ ማደግ ለኔ መበረታቻ ነው ብሎ የሚያስብ ነጋዴ እንዲኖር፣
መጦሪያዬን ፎቅ ልስራ ሳይሆን ብዙ ዜጎች የሚቀጥር ፋብሪካ ልገንባ የሚል ባለሃብት ማየት፣
እኔ በምከፍለው ግብር የሚሰራ የመንግስት ሰራተኛ በቅጡ ሊያስተናግደኝ መቻል አለበት ብሎ የሚያስብ እጁን ኪሱ ከመክተቱ በፊት፣
ፖለቲካው
የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች ተፈተው በነጻነት ሲጽፉ፣ ሲቀሰቅሱ፣ ፓርላማ ገብተው ሲከራከሩ ማየት፣
ሁሉም የሚስማማበት ምርጫ የትም ዓለም ላይ ይደረጋል ብዬ አላስብም ነገርግን የኢትዮጵያን ሕዝብ በብዛት ያሳመነ ምርጫ ተደርጎ ተሸናፊው ቡድን አሸናፊውን እንኳን ደስ አለህ ብሎ ለህዝብ ጥቅም ሲል አብሮት የሚሰለፍበት ምርጫ ማየት፣
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁሉም መስክ (ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች)  እኩል ተጠቃሚነትና እኩል እድል ኖሮት ማየት፣
ዘርና ጾታ በተፈጥሮ የሚገኙ እንጂ በዕድል ወይም በአጥንት ወይም በዕውቀት የማይመጡ መሆኑን አውቆ በሁለቱ መገለጫዎች ምክንያትነት ብቻ የበላይ ነኝ ብሎ የማያስብና ከብሔሬ በፊት ኢትዮጵያ ትቀድማለች ብሎ የሚያስብና ኢትዮጵያ የኔ ናት የሚል ትውልድ ማየት፣
ነጻ ፕሬስ ኖሮ ለሕዝቡና ለሀገሪቱ ጠቃሚ የሆኑ ሀሳቦች እየወጡ የሚፋጩበት፣ ለእስኪሪፕቶን በእስኪሪፕቶ አንጂ በጥይትና እስር ምላሽ የማይሰጥባትን ኢትዮጵያ ማየት፣
ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እንጂ ማስፈራርያ ብሎም የግል ጥቅም ማፍሪያ ያልሆነባትን ኢትዮጵያ ማየት፣
ተቃዋሚ ስለተባሉ ብቻ መንግስት የሚሰራውን በሙሉ መቃወም አለብኝ ብሎ የማያስብና የመሃል መንገድም አለ ብሎ የሚያስብ ተቃዋሚ ተፈጥሮ ማየት፣
ዳያስፖራ ፖለቲከኞች በሰንሰለት እንደታሰረ ኃይለኛ ውሻ ውጭ ሆናችሁ ወደ ቤት ከምትጮሁ እስኪ የሞቀ የውጭ ኑሯችሁን ከቻላችሁ ይዛችሁ ካልቻላችሁ እጃችሁ ላይ ያለውን ይዛችሁ ኑና እንታገልልሃለን የምትሉትን ሕዝብ በዕውቀታችሁና በገንዘባችሁ ችግሩን ፍቱለት፣ ችግር ሁሉ ስልጣን በመያዝ ብቻ አይፈታምና፡፡በጭፍኑ መንግስትን መቃወም ብቻ ለገዥው መንግስት ጥሩ የፕሮፖጋንዳ ግብዓት እየሆነ ስለሆነ መሬት ይዛችሁ መክራችሁበት ወደ ሀገራችሁ መጥታችሁ ወይም ባላችሁበት ለሀገራችሁ የምትችሉትን አርጋችሁ ማየት፣
መንግስት ለሕዝብ የሚጠቅም ፖሊሲና ስትራቴጂ ሊቀርጽ ሲያስብ ከፖለቲካ ባሻገር የመስኩን ልሂቃን እያማከረ የሚዘጋጅባት ኢትዮጵያን ማየት፣
ግንባርና ቀንድ እያሉ ጎጥ እየፈጠሩ ሀገርን የሚያክል ነገር እንደ አቡጀዲ ለመቅደድና ለመገንጠል የሚያስቡ ኃይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው በሰለጠነ ሰው ስረዓት ሲነጋገሩ ማየት፣
ማህበራዊ ጉዳዮች
ሃይማኖት የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ ሳይሆን ህዝብን ግብረ ገብነት ማስተማሪያ ሆኖ ማየት፣
የእምነት ተከታዮች በጎሪጥና በጥላቻ የሚተያዩባት ሳይሆን አንዱ ለሌላው የወንድሜን ሃይማኖት አትኩበት ብሎ ለጎረቤቱ ዘብ የሚቆምባት ኢትዮጵያን ማየት፣
ሌላው በሰራው ጀግንነት ቁጭ ብሎ የሚኩራራ ትውልድ ሳይሆን ለታሪኩ ክብር ሰጥቶ ካለፈው ጥሩውንም መጥፎውንም መርምሮ የሚማር ትውልድ ተፈጥሮ ማየት፣
የራሱን ታሪክ ለማጉላት ብሎ ያለፈውን የሚያጨፈግግ መንግስት ሳይሆን ካለፈው ስህተት ተምሮ ለመጭው ታሪኩ የሚጠነቀቅ ብሎም ባለፈው ታሪካችን ውስጥ ያበሩ (ብልጭ ያሉ) መልካም ጅማሮውችንና ታሪኮችን አክብሮ ለትውልድ ማስተላለፍ፣
እያለ እያለ መልካም መልካሙን ተመኘሁ እናንተስ?