"ጎበዝ!ይሄ ሰርክ በኢቲቪ እና በመንግስት ራድዮናዎች ላይ ያሉት ትንታግ ካድሬዎቻችን የሚሰብኩን እና ወቅት እና
ሁኔታዎችን ጠብቀው ወደ ቴሌቭዥናችን መስኮት ብቅ የሚሉት እነዛ የኢቲቪ "አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች" የሚምሉበት፣
ቃል የሚገቡበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይ ጉዳይ እየቆየ ሲመጣ ያሳስበኝ ጀምሮአል። እያሳሰበኝ ያለው ግን በፀረ
ሰላም እና በፀረ ልማት ሀይሎች የሚደርስበት ተፅፅኖ ሳይሆን ይሄ ራዕይ በኔ ዕይታ ታሪክን በማዛባት ላይ እየፈጠረ
ያለው ተፅፅኖ ነው። በተለይ ኢቲቪን አዘውትረው የሚከታተሉ እና ስለ ሀገራቸው የቀደመ ታሪክ የማንበብ ወይም የማወቅ
እድል ያልተፈጠረላቸው ብላቴኖች በሀገራችን አሁን እየታዪ ያሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በታሪካችን
ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰቡ፣ የተወጠኑ እንዲሁም ከ1983 በፊት የነበሩት መሪዎች ሀገራቸውን ለማዘመን ምንም ያልጣሩ፣
እንዲሁም ከድህነት ለማውጣት ምንም ያልሞከሩ ቢያንስ እንኩዋን ራዕዪ ያልነበራቸው የሚመስላቸው ይመስለኛል። አሁን
እንዲህ ስል ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትራችን የነበራቸውን ቁርጠኝነት እና የሰሩዋቸውን ስራዎች ማንኩዋሰሴ
አይደለም። ስለዚህ ለማይረባ የፖለቲካ ትርፍ ታሪክን ባታዛቡ መልካም ይመስለኛል። ምናልባት እዚህ ጋር ታሪክን
ማዛባት የሚለው ነገር አልከበደም የሚል ጥያቄ ሊኖር ይችላል፤እንደኔ እምነት ከብዙ የታሪክ ገፆች መሀል የወደዱትን
ማግዝፍ ያልወደዱትን ደግሞ እስከነመፈጠሩ መርሳት ታሪክን ማዛባት ነው። ስለ በግ ጥሩነት ለማውራት ፍየልን ማንቁሸሽ
አያስፈልገንም በግ ብቻዋን መቆም ትችላለች እና።የኔ ስሜት የብቻዬ ይሆን ወይስ እናንተም ታዝባችሁታል?
አስተያየታችሁን ጣል አድርጉ::
ኤፍሬም
አፈወርቅ