ይህን ርዕስ የመረጥኩት
ፌስቡክ (ገጸ-መጽሀፍ ይለዋል አንድ ወዳጄ) ላይ በብዙ ሰዎች ሼርና ላይክ የተደረገውን ከዚህ በታች የሚገኘውን ፎቶ ከተመለከትኩ
በኃላ ነው፡፡ የምስል ቅንብሩ የደብተራው ጸጋዬ እንደሆነ ምስሉ ላይ ይገልጻል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የጻፍኩትን አንብባችሁ የፈለጋችሁትን
በሉ፡፡
“የድሮ ተማሪ ጥያቄዎች” ተብለው የተጠቀሱት
1. መሬት ለአራሹ፡- ይህ ጥያቄ በጣም ትክክልና ወቅታዊም እንደነበረ አምናለሁ አንብቤ
ከተረዳሁት፡፡ ግን በአሁኑ ወቅት መሬቱን የያዘው በብዛት ማለት ይቻላል በተለይ ሳኡዲ ስታር ሳይመጣ እራሱ እራሹ ነው፡፡ የሚያርሰውም
ለግሉ ነው እንጂ ለ“ነፍጠኛው ገዥ መደብ አይደለም” (ት.ያ. (ትንሽ ያስቃል)) ስለዚህ ይህን ጥያቄ በዚህ ሰዓት ከማንሳት ኮብልስቶን
መፍለጥ ይሻላል፡፡
2. የምርጫ ድምፃችን ይሰማ፡- ሲጀመር ይሄ ጥያቄ
በምን ቀመር የድሮ ተማሪዎች ጥያቄ ሊሆን እንደቻለ አልገባኝም፡፡ ምክንያቱም የድሮ ተማሪ የተማሪ ተወካይ ከመምረጥ ሌላ የምን ምርጫ
ያርፋል? ሲቀጥል ጥያቄው የተጠየቀው በምርጫ 97 ወቅት ነው፣ ምላሹም “በለው ማን አንሳ አለው?” ሆኖ ያሁሉ ወጣት ሲሞት፤ አካል
ጉዳተኞች ሲሆን፣ በጣም ብዙዎች ደግሞ ሲጫሩ (እዚህ ላይ በዛ ወቅት የተባረሩ ተማሪዎች የትም ሲቀሩ አባከና የሚላቸው አጥተው ያባረራቸው
መንግስት ራሱ መልሶ ጸጸት ልባቸውን ስለመዘመዘው በኮብልስቶን ጠረባ ላይ እንዲሳተፉ ፈቀደላቸው (ት.ያ)) ዞር ብሎ የት ወደቁ
ያለ ማነው፡፡ ስለዚህ የዛኔ በአደባባይ ወንድሙ ሲገደል፣ አካል ጉዳተኛ ሲሆን፣ ዝዋይና ዴዴሳ ሄዶ እሬቻውን ሲበላ ማንም ዞር ብሎ
እንዳላየው እያየ ለምን አርፎ አይማር፡፡ ደግሞ አሁን እንደ ድሮው ሄዶ መምረጥ ቀርቷል አሉ በማርያም እየተባለ እየተደወለ እየመረጠ
ለምን ይቃወም፡፡ ይልቅ በበቀደሙ የአካባቢ ምርጫ እለት ካርድ የወሰዱት ሰዎች ጋር ሲቆዩ ይደወል ነበረ መሰለኝና አንዱ ሰውዬ አስቸኳይ
ስራ ስለነበረበት ቢሮ ገብቶ እየሰራ ደወሉለት ከዛ “እሺ መጣለሁ ትንሽ ስራ በዝቶብኝ ነው” ይላቸዋል፣ አንድ ሰዓት ቆይተው ደግመው
ይደውላሉ “አሁንም ስራዬን አልጨረስኩም በቃ እስከ ማታ ስለሆነ ወደ 11፡00 ሰዓት ላይ መጥቼ መርጣለሁ” ይላቸዋል፣ ይሄኔ ደዋዩ
ልጅ ከላይ ትዕዛዝ ተሰጥቶት መሰለኝ ምን ቢል ጥሩ ነው “ካልተመቾት ይንገሩንና ኮሮጆ ይዘን መጥተን ባሉበት እናስመርጦት” አለው፡፡
እናቴ ትሙት ኮሮጆ ይዤ ልምጣ ሳይሆን መጥተን ፒክ እናርጎት ነው እንጂ ያለው ሌላውን እውነቴን ነው ካላመናችሁኝ የነገረኝን ሰውዬ
ላገናኛችሁ፡፡
3. አንድ ሀገር አንድ ህዝብ፡- እውነት ለመናገር
ፌደራሊዝም አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት አዲስ አበባ ላይ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል ብል ያመዋል እንዴ የሚለኝ ሰው እውነቱን
ነው ከሚለኝ ያንሳል ብዬ አስባለሁ፡፡ በርግጥ ሁሉም ዜጋ በራሱ ቋንቋ መማሩንና በራሱ ተወላጅ መተዳደሩን ከማንም በላይ ብደግፍም
አንድ ሀገር ውስጥ እስከኖርን ድረስ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ ቢሰራ አሪፍ ነበረ፡፡ ሳስበው ከአሁን በኋላ
አሃዳዊት ኢትዮጵያ ትኖራለች የሚል ግምት ፈፅሞ የለኝም ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ከአሁን በኃላ መሰራት አለበት ብዬ የማስበው
እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በክረምት ወቅት ወደ ቀዬው ተመልሶ ድንጋይ ከሚያሞቅ (አብዛኞቻችን እንደዚህ ነን) ከተወለደበት አካባቢ
ውጭ ሄዶ ህዝብ እንዲያገለግል ቢደረግ ልክ በደርግ ጊዜ ተጀምሮ እንደነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ይጎለብታል ብዬ አስባለሁ፡፡
ማለትም የኤልከሬውን ልጅ እንትጮ ልኮ ከህዝቡ ጋር እየኖረ እንዲሰራ ቢደረግ ነገ ተመርቆ ወደ አካባቢው ቢሄድ ስራ ላይከለክሉት
ይችላሉ፡፡ ለነገሩ ይህን ሃሳቤን ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ ሸገር ላይ ባረጉት ጨዋታ ጥሩ አርገው አብራርተውታል፡፡
4. አካዳሚክ ነጻነት ይከበር፡- የአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አካዳሚክ ነጻነት የሚረጋገጠው ተቋሙ የሚከተሉትን ነጥቦች በአካዳሚክ መሰረት
(Academic Grounds) ላይ ሆኖ መወሰን ሲችል ነው፡-
a.
ማነው ማስተማር ያለበት/ ማስተማር የሚችለው
b.
ምን ማስተማር አለብኝ
c.
እንዴት ማስተማር አለብኝና
d.
ማንን መቀበል አለብኝ
ስለዚህ
እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ወይም የመመለስ አቅም ያለው የትምህርት ተቋም አሁንም ድሮም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ስለማይመስለኝ
ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔና መሰሎቼ አካዳሚክ ፍሪደም ብትሉን ትፈላሰፋለህ እንዴ በል አርፈህ ነገ ከማን እንደምንሰራ (እንደምንኮርጅ)
አስብ ስለሆነ መልሳችን ጥያቄውን ለማንሳት አንደፍርም፡፡ ምክንያቱም እንኳን እኛ ተማሪዎቹ መምህራኖቻችን አያርፉትማ በተለይ ደግሞ
አዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያሉት ጠቅላላም ሆነ አካዳሚክ ዕውቀታቸው ወፍ የለም፡፡
5. ሀገር አትገንጠል፡- ካስተዋላችሁ አሁን ዩኒቨርሲቲ ያለው ወጣት አኮ ሀገር ከተገነጠለች
ነው ነፍስ ያወቀው (የሚያስተውል ቀልብ ያለው ሲኖር አይደል) ስለዚህ ይሄንንም ጥያቄ አናርፈውም፡፡ “የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እስከሆነ
ድረስ ስለ ሀገሩ አንብቦ ነው መረዳት ያለበት” የሚል ካለ ደግሞ መጽሀፍ ከማንበብ መገንጠል የሚቀናው ተማሪ ስለሆነ መስሚያው ጥጥ
ነው በተለይ አንብብ ለሚለው ሰው፡፡
6. በዘርና ጎሳ አትከፋፍሉን፡- በዘርና ጎሳ ተከፋፍሎ
የመጣ ተማሪ እንዴት ብሎ ነው አትከፋፍሉን የሚለው ደግሞ ካልተከፋፈልክ ከሁሉም ተገለህ ብቻህን ሜዳ ላይ ልታወራ ነው፡፡ ስለዚህ
አርፈህ መመሳሰል ነው፡፡ የአዲስ አበባ ልጅ ከሆንክ ብቻ ነው የዘርና ጎሳ ነገር ብዙ የማያሰጨንቅህ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ሆነህ
ነዋ የምታድገው አንድ ቋንቋ አውርተህ፤ ስምህ የጀግና ወይ የመጽሀፍ ቅዱስ ወይ የቁርአን ወይ የፈረንጅ ነው በምን ትለያያለህ፡፡
ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነኝ በቀድሞ ስሙ የንግድ ስራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) በአዲሱ ደግሞ የንግድ ስራ ት/ቤት ነው፡፡ እዛ ድሮም ብዙ
የክፍለ ሀገር ተማሪ አይገባም አሁንማ ጭራሽ የክፍለ ሀገር ተማሪ አይገባም የመጀመሪያ ምርጫው ካልሆነ (ዶርምና ካፌ ስለሌለው ነው)
እና እዛ ሄዳችሁ ዘር፣ ጎሳ ምናምን ብትሏቸው መስሚያቸው ድፍን ነው (ከክፍለ ሀገር መጥቶ ፕሪፓራቶሪ አዲስ አበባ ተምሮ ካልገባ
በስተቀር)፡፡
“የዘንድሮ ተማሪ ጥያቄዎች” ተብለው የተጠቀሱት
1. ክሬዚ ዴይ/ ዋተር ዴይ/ ክራቫት (ጀንትል) ዴይ ይከበር፡- የድሮ ተማሪ ሲጀመር
ጀንትል ስለሆነ የራሱን ቀን ማክበር አያስፈልገውም፡፡ የአሁን ተማሪ ደግሞ ክሬዚ ስለሆነ የራሱን ቀን ማክበር አያስፈልገውም፡፡
ከነዚህ መቅደም ያለባቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ማንም አይክድም ነገር ግን እንዚህ ተማሪዎች ልጆች ናቸው በዛ ላይ ከዩኒቨርሲቲ እንደወጡ
አብዛኞቹ የመንግስት (የቢሮም ኮብልስቶን መደርደርና መፍለጥም የመንግስት ስራዎች ስለሆኑ ነው) ስራ ላይ ነው የሚጠመዱት ስለዚህ
አሁን ቺል አርገው ቢያልፉ ብዙ አያስቀይምም፡፡ ኧረ ደግሞ ማነው ከልክሎ የሚያውቀውና ነው ይከበር ብለው የሚጠይቁት፡፡
2. የዳቦ ግራም ቀነሰ፡- እውነታቸውን ነው ታድያ አፈር ቅጠል የማይል ዳቦ እየሰጡ በሱም ብሶ
ውስጡ ባዶ ሲሆን ይከፋል፡፡ ኮስት ሼሪንግ ተብሎ በአዲስ አበባ ኑሮ 300 ብር ብቻ እየተሰጠህ ከክፍለ ሀገር እንደ መምጣትህ ቤት
ተከራይተህ ቀለብህን ችለህ ኑር ሲባል መጮህ ይነሰው እንዴ ጎበዝ የዳቦና ኮስት ሼሪንግ ጥያቄ አንድ ነው ብዬ ነው፡፡ ደግሞ የድሮ
ተማሪ ዶሮ ወጥ እየበላ፣ ልብስና ጫማ እየተሰጠው አለፍ ሲልም የኪስ ገንዘብ እየተሰጠው እየተማረ ልቡን ጥጋብ ነፍቶት ነው መንግስት
ላይ ቡራ ከረዩ የሚለው (ደሞ የዛ ዘመን መንግስት የዋህ ነው በጭስ አልሆን ካለው መሪውን መድፋት ካልሆነ እንደዚህ ዘመን ስርዓት
የስናይፐር ጥይትን እንደ ነጭ ሽንኩርት አፍንጫህ ውስጥ አይከተውም)፡፡ ያሁን ተማሪ በኮስት ሼሪንግ (ማለትም በገንዘቡ) እየተማረ፣
እየተመገበ፣ እየኖረ ለምን ብሎ እየከፈለ አገልግሎት ይቀነስበታል፡፡
3. ምግቡ አልጣፍጥ አለን፡- ይህ ጥያቄ ከላይኛው ጋር የተያያዘና ተመሳሳይ ነው፡፡ መልሱም አጭር
ነው፤ በገንዘቡ ገዝቶ እየበላ ስለሆነ ጣፋጭ ምግብ ሊቀርብለት ይገባል፡፡
4. የጎሳዬ ልጅ ተደበደበ፡- የተሸወዱት ነገር እንዲህ ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ የእገሌ ልጅ ተደበደበ
አይደለም እገሌ ተደበደበ ብትሉት እኔ ምን አገባኝ ትምህርት ቢዘጉልን ነበረ አሪፍ ካልተዘጋማ ከፈለገ ለምን እንደ ሽንኩርት ባናቱ
ተክለው ወፌ ላላ አይገርፉትም ነው የሚላችሁ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ (አጋጣሚ አቃጣሪ ነው ይላል ጓደኛዬ) ይህን ጥያቄ ቢያነሱ እንኳ
ልጁ ስለተደበደበ ሳይሆን የልጁን መደብደብ ምክንያት ሆኖ ትምህርት እንዲቋረጥ ነው፡፡ እመኑኝ፡፡
5. የDSTv ካርድ በወቅቱ አልተገዛም፡- በነገራችን ላይ እኔ
በአካል ካየኋቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአዲስ አበባና የጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች በነጻ ነው ኳስ የሚያሳዩት፤ እንደውም ጂማ
ዩኒቨርሲቲ በየብሎኩ ነው ቴሌቪዥን ያለው መሰለኝ አዲሱ የኢንጂነሪንግ ዶርሚተሪዎች ጋር፡፡ ተማሪው በትርፍ ሰዓቱ ኳስ ቢከታተል
አሪፍ ነው በርጫና ቅምቀማ ላይ ከሚሰየም፡፡ ጥያቄው ለምን ያያል እንዳልሆነ ይገባኛል የመጣበት አካባቢ የመሰረተ ልማት ግንባታ
ይካሄድ ብሎ እንደ መጠየቅ ነገ እዛው ገጠር ጭለማ ውስጥ ተመልሶ እንሚገባ ረስቶት ስለ አንድ ነጫ ጭባ ቆዳ ገፊ (ለምሳሌ ክ.
ሮናልዶ) እርግጫ መቋረጥ ይብከነከናል ነው፡፡ በአጭሩ ማለት የፈለጋችሁት ገብቶኛል ከኳስ ጋር በተገናኘ ብዙ ጊዜውን ከሚያሳልፍ
ቢያነብ፣ ቢጠይቅ፣ ቢከራከር ለራሱም ለሀገሩም ይጠቅማል፡፡ እስማማለሁ፡፡
ባጠቃላይ ማለት የምፈልገው
ትውልዱን በመውቀስ፣ የጥፋተኝነትና የሀሞተ ቢስነት ስሜት እንዲያድርበት በማድረግ ወደ ምንፈልገው አቅጣጫ መምራት እንችላለን ብላችሁ
ካሰባችሁ ፉርሽ ናችሁ፡፡ ጭንጋፍ ሲባል ነው ወይስ አንበሳ ሲባል ነው ትውልዱ የሚበራታታው? መልሱን ለራሳችሁ፡፡ ደግሞ ከሁሉ በላይ
የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስለሆነ ብቻ የግድ ተቃዋሚ መኾን አለበት ያለው ማነው? ከላይ እንደጠቀስኩት ቅንጅት ሲወዳደር እንዳለ ሽማግሌዎች
ናቸው ለስልጣን የተወዳደሩት አደባባይ ወጥቶ የሞተው ግን አንዲት ጥቅም ያለገኘው/የማያገኘው (በመንግስትም በተ ቋሚዎችም) ወጣቱ ነው ስለዚህ የወጣቱን ደመ ሞቃትነት ተጠቅማችሁ ስልጣን መጨበት
የምትፈልጉ አካላት በተለይም ዳያስፖራ ፓለቲከኞች እባካችሁ ለወጣቱ እዘኑለት (አሜሪካ ዱቅ ብላችሁ የግብፅን አብዮት ኢትዮጵያ ላይ
እናስጀምር የምትሉ ቦለቲከኞች የግብፅ አብዮት የተጀመረው ውጭ ባሉ ግብጻውያን ሳይሆን ሀገር ውስጥ ባሉ ሁሉም ዜጎች ነው)፡፡
ዛሬ በጣም ብዙ ሊጻፍባቸው
የሚችሉ ርዕሶች አንስቼ ያባከንኩ የሚመስላችሁ ሰዎች (እኔ እንደዛ ስለመሰለኝ ነው) እስቲ እናንተ በታትናችሁ ፃፉባቸው እኔም ሾጥ
ካረገኝ እመለስባቸው ይሆናል፡፡ በተረፈ ግን ይሄ የፍሬዘር ምልከታ ስለሆነ የፈለኩትን በሚመቸኝ መልኩ ጽፌያለሁ፡፡ ቋንቋዬ ካልተመቻችሁ
ይቅርታ ይሄ የዳንኤል ክብረት ብሎግ አይደለም እንዳልመፃደቅ (እንደ ስድብ እንዳይቆጥሩብኝ) ወይም የዳንኤል ብርሀኔ ብሎግ አይደለም
የፖለቲካ/ዲፕሎማሲ ቃል የሚጠቀም፣ ይሄ የኔ ብሎግ ነው፣ እኔ ደግሞ እንደማወራው መጻፍ ነው የምፈልገው ብዙዎቻችን ስንጽፍ፣ በቴሌቪዥንና
በሬድዮ ስናወራ አጻጻፋችንና አነጋገራችን ይለያያል ድራማና ፊልሞቻችንን ጨምሮ፡፡ እኔ ደሞ ይሄ ስታይላችሁ አይመቸኝም፣ እንደማወራው
መጻፍ ስለምፈልግ፡፡ ይህች ፍንዳታ ምነው አለሁ አለሁ አለች ካላችሁኝ አቦ ይመቻችሁ እንዳለሁ ስላያችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የፈለጋችሁትን
ብትሉ ደስ እያለኝ እቀበላለሁ፡፡
ፍሬዘር ማሩ